መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

Song of Songs — ምዕራፍ 1

1ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።
✝
2በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና።
✝
3ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ።
✝
4ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ ቤቱ አገባኝ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፤ በቅንነት ይወድዱሃል።
✝
5እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች።
✝
6ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና፤ ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም።
✝
7ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቅትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ?
✝
8አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ።
✝
9ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ።
10የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው።
✝
11ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን።
12ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ።
✝
13ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
✝
14ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው።
✝
15ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው።
✝
16ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው።
✝
17የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።
✝